የተቀናጀ የግጦሸ አጠቃቀምና · ልማት ተግባርን በማሳደግ...

19
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የግብርና ሚኒስቴር የተቀናጀ የግጦሸ አጠቃቀምና ቁጥጥር ስትራቴጂ አዲስ አበባ ነሀሴ 2004 ..

Upload: others

Post on 14-Mar-2020

33 views

Category:

Documents


1 download

TRANSCRIPT

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ

የግብርና ሚኒስቴር

የተቀናጀ የግጦሸ አጠቃቀምና ቁጥጥር ስትራቴጂ

አዲስ አበባ

ነሀሴ 2004 ዓ.ም.

ማውጫ

1. መግቢያ…………………………………………………………………………………… 1

2. የስትራቴጂ አስፈላጊነት…………………………………………………………………… 1

3. ልቅ ግጦሽን ማስቀረት የሚኖረው ጠቀሜታ…………………………………………….. 2

3.1 አካባቢያዊና ማኀበራዊ ጠቀሜታ…………………………………………………… 2

3.2 የእንስሳት ምርታማነትን ለመጨመር ያለው ጠቀሜታ……………………………. 3

3.3 ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጠቀሜታ…………………………………………………. 4

4. ልቅ ግጦሽን በማስቀረት ውጤታማ የሆኑ ተሞክሮዎች………………………………… 6

5. ልቅ ግጦሽን የማስቀረት ተግዳሮቶች…………………………………………………….. 8

5.1 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች………………………………………………. 8

5.2 ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ተግዳሮቶች……………………………………………… 8

6. የስትራቴጂው አቅጣጫዎች………………………………………………………………. 9

6.1 ተከልለው እንዲያገግሙ በተደረጉ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች

በተከናወኑባቸው አካባቢዎች የመኖ ምርታማነት የማሳደግ ስትራቴጂ…………….10

6.2 በእርሻ ማሳዎች ላይ የምንከተለው ስትራቴጂ……………………………………… 11

6.3 የእንስሳት ቁጥር የመቀነስና ምርታማ ዝርያዎችን የማስፋፋት……………………...12

6.4 የእንስሳትና የመኖ ቴክኖሎጂዎችን አቀናጅቶ የመተግበር…………………………. 13

6.5 ሌሎች አገልግሎቶችን አቀናጅቶ ተግባራዊ የማድረግ……………………………… 14

7. የስትራቴጂው የአፈጻጸም ስልቶች…………………………………………………………. 14

7.1 የህብረተሰቡን ሙሉ ተሳትፎ እና ስምምነት ላይ በመመሥረት የመተግበር……… 14

7.2 በየደረጃው ላሉ አስፈጻሚ አካላት ግንዛቤ መፍጠር………………………………… 15

7.3 መልካም ተሞክሮዎችን የማለዋወጥ ስልት………………………………………… 15

7.4 በየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ማድረግ……………….. 15

7.5 የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ መተግበር………………………………… 16

7.6 ተግባራዊ ሥራው በዕቅድ እንዲመራ ማድረግ……………………………………… 16

8. የስትራቴጂው የአፈጻጸም መርሀ ግብር…………………………………………………… 17

1. መግቢያ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቤት እንስሳት ቁጥር አላት፡፡ 40.3 ሚሊዮን የቀንድ ከብት፣ 25.1 ሚሊዮን

በግ፣ 22.3 ሚሊዮን ፍየሎችና 1.71 ሚሊዮን ግመሎች ሲሆኑ የእንስሳት እርባታ ዘዴውም

በሦስት ዓይነት ሊገለጽ ይችላል፡፡ እነሱም በአርሶ አደሩ፣ በአርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ

አደሩ ሲሆን የእንስሳት አረባብ ዘዴውም ዘመናዊ ባለመሆኑና ምርታማነቱ እጅግ አነስተኛ

ሰለሆነ ሀገራችን ካሏት ከፍተኛ የእንስሳት ቁጥር ጋር በዘርፉ ተመጣጣኝ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም

ማግኘት አልቻለችም፡፡ ይህም ሊሆን ካስቻሉ ምክንያቶች አንዱ ከእንስሳት መኖ ምንጮች

ከፍተኛውን እጅ የያዘው የተፈጥሮ ግጦሽ በመሆኑና ይህንንም የምንጠቀመው በልቅ ግጦሽ

በመሆኑ የሚለው የሚጠቀስ ነው፡፡ በተጨማሪም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሕዝብ

ቁጥር የግጦሽ ቦታዎችን ለእርሻ መሬት በማዋሉ የግጦሽ ቦታዎች መጠናቸው እያነሰ

መምጣቱ፣ ያሉን የግጦሽ ቦታዎችም ቢሆኑ ከመጠን በላይ በመጋጥ በመራቆታቸው፣ የደን

መጨፍጨፍ፤ የአፈር መሸርሸርና የበረሃማነት መስፋፋትን እያስከተለ እየሄደ መሆኑ ነው፡፡

ሀገራችን በእንስሳቱ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማግኘት ያስችላት ዘንድ

እና ተፈጥሮአዊ ሚዛንን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ዘላቂ ልማትና እድገት

ለማምጣት የሚያስችል በኢትዮጵያ ልቅ ግጦሽን በሂደት ለማስቀረት እንዲቻል የተቀናጀ

የግጦሽ አጠቃቀምና ቁጥጥር ስትራቴጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

2. የስትራቴጂው አስፈላጊነት የተፈጥሮ ሀብት መመናመን ቸግሮችን መፍትሄ ለመስጠት፣

የመኖ ልማት ላይ አስፈላጊውን የቴክኒክና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት ምርታማነቱን

ለማሻሻል፣

እንደየስነምህዳሩ ተስማሚ የሆኑ የመኖ ዕፅዋት ዓይነቶችና የማልማት ስተራቴጂዎችን

በመጠቀም በዘላቂነት በማምረትና ለእንስሳት በቂ መኖ በማቅረብ የእንስሳቱን ጥቅም

በማሻሻል ምርታማነታቸውን ከፍ ለማድረግ፣

የግጦሽ ቦታዎችን በሚገባ በመንከባከብና በማልማት ምርታማነታቸውን ለመጨመርና

የተፈጥሮ ሚዛን በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ፣

የወቅቱ የዓየር ንብረት ለውጥ እያመጣ ያለውን ችግር ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን

መውሰድ እንዲቻል፣

በሀገሪቱ ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በህብረተሰቡ ንቅናቄ

እየተሠራ ያለውን ሥራ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የለሙትንም ቦታዎች አጠቃቀም ፈር

በማስያዝ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ከላይ የተጠቀሱትን የልቅ ግጦሽ የማስቀረት ስትራቴጂ

2

አስፈላጊነት በማገናዘብ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግሥት ለተለያዩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች

በተለይ ለመሬት አጠቃቀም ከወጡ ፖሊሲዎች እና የደን ልማት ጥበቃና አጠቃቀም

ፖሊሲና ስትራቴጂ ዘለቄታ ባለው መንገድ በጥቅም ላይ ለማዋል ከዚህ በታች የቀረበው

ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል፡፡

3. ልቅ ግጦሽን ማስቀረት የሚኖረው ጠቀሜታ

ልቅ ግጦሽ ማለት የእንስሳት ምግብን አስቦና ገምቶ ከማምረትና አዘጋጅቶ ከማቅረብ ይልቅ

እንሰሳቱን በማንኛውም የመሬት አጠቃቀም ላይ ያለ ገደብ በማሰማራትበመሬቱ ላይ የተገኘውን

መርጠው በፈለጉበት ደረጃ እንዲግጡ የማድረግ ተግባር ነው:: ይህ ተግባር በሀገራችን ከብዙ ሺህ

ዓመታት ጀምሮ የእንስሳት መዋያ እንደ ልብ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ የተለመደ የእንስሳት አረባብና

አመጋገብ ዘይቤ ሆኖ ቆይቷል፡፡የእርሻ ሥራ እየተስፋፋ በመምጣቱ ሳቢያ ለእንስሳት ግጦሽ

የሚያገለግሉ ቦታዎች እየተመናመኑና እንዲሁም በእያንዳንዱ ቤተሰብ የሚያዘው የእንስሳት

ቁጥር እየጨመረ መምጣት የእንስሳቱን የምግብ ፍላጐት ለማሟላት በማይችልበት ደረጃ ላይ

ተደርሶል:: በነዚህም ምክንያቶች የተፈጥሮ ሀብት መመናመንና የመሬት መራቆት እያስከተለ

የሚገኝበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ከዚህም ባሻገር የልቅ ግጦሽ ተግባር የእንስሳትን ምርታማነት

የማያሳድግ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንስሳቱ የሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እየተዳከመ

የሚሄድ ከመሆኑ በተጨማሪ ሌሎች ማህበራዊና አካባቢያዊ ችግሮች የሚያስከትል ነዉ:: በመሆኑም

ይህንን ልማዳዊ አሠራር ለማስተካከል የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርፆ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ የልቅ

ግጦሽን ማስቀረት የሚኖረውን ዘርፍ ብዙ ጥቅሞች በሚከተሉት ዋና ዋና ማሳያዎች መግለፅ

ይቻላል፡፡

3.1 አካባቢያዊና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ

በልማት ዕቅድ ላይ ያልተመሠረተ የእንስሳት አመጋገብ፤የመኖና ግጦሽ አያያዝ ተግባር እንስሳት

ያለገደብ ያገኙትን እንዲግጡ የሚያደርግ ሥርአት በመሆኑ ከጊዜ ወደጊዜ እንስሳቶቹ የዋሉበት

መሬት የሚሰጠውን የመኖና ግጦሽ መጠንና ዓይነት እየቀነሰ ከመምጣቱ ባሻገር ከእንስሳቱ ቁጥር

ጋር ያልተገናዘበ በመሆን ከመጠን በላይ በመጋጥ መሬቱ የእጽዋት ሽፋኑን በማጣት ራቁቱን

ያስቀረዋል፡፡ ይህ በመሆኑም መሬቱ ለተለያዩ ለአፈር ክለት መንስኤ ለሆኑ አደጋዎች ይጋለጣል፡፡

የአፈር በውኃና በንፋስ መሸርሸር፣የአፈር ለምነትን ከማሳጣቱ ባሻገር እርጥበት ወደ መሬት ዉስጥ

እንዳይገባ ያደርጋል፤ከነዚህም በተጨማሪ በታችኛዉ የተፋሰስ አካባቢ የጐርፍ አደጋን

ይጨምራል፡፡በልቅግጦሽ ስርአት እንስሳት የሚስማማቸውን እፅዋት እየመረጡ ስለሚግጡ ጠቃሚ

የዕፅዋት ዝርያዎች በሚደርስባቸው ከመጠን በላይ የመጋጥ አደጋ ምክንያት ከአካባቢዉ ይጠፋሉ፡፡

የሚቀሩትም እጽዋት በእንስሳቱ የማይፈለጉና ምናልባትም በአንፃራዊነት ጐጂና ጥቅም የማይሰጡ

3

ዝርያዎች በመሆን አካባቢውን እንዲወሩ እድል ስለሚፈጥር መሬቱ ጥቅም አልባ ይሆናል ፡፡

በአጠቃላይም የስነ-ምህዳራዊ ሚዛን መዛባት የሚያስከትል በመሆኑ በዕቅድ ያልተመራ ልቅ

ግጦሽን በማስቀረት በምትኩ ስርአት ያለው የእንስሳት መኖ ልማት ዝግጀትና የግጦሽ ቦታዎችን

መንከባከብ ስራዎች እዉን ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በሌላ መልኩ እንስሳት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ በተለይ ደግሞ እርጥበት በሚኖርበት ጊዜ

በኮትያቸዉ በሚፈጥሩት መረጋገጥ ጫና ምክንያት የአፈርን ተፈጥሮአዊ ጥንካሬ ስለሚያሳጡት

እንዲሰባበርና ለተጨማሪ በውኃ ና በንፋስ የመታጠብና የመሸርሸር አደጋ ያስከትላሉ፡፡በተጨማሪ

የእንስሳቱ ቁጥጥር የለሽ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ በሚደረግበት ቦታ የአፈር መጠቅጠቅ ይከሰታል::

በዚህም ምክንያት በዝናብ ወቅት ወደ መሬት ውስጥ የሚገባውን የውኃ መጠን ይቀንሳል፤ በዚህ

ሳቢያም የልቅ ግጦሽ ሰለባ በሚሆኑባቸው አካባቢዎች እና ምናልባትም በሌሎች ሥፍራዎች

የምንጭ መድረቅ፣ የወንዞች ፍሰት መጠን መቀነስ ወይም መድረቅ፣ የከርሰ ምድር ውኃ መራቅ

እና የመሳሰሉት አካባቢያዊና ሥነ-ምህዳራዊ ሚዛን መዛባት ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ልቅ ግጦሽን

መቆጣጠርና ሥርዓት ማስያዝ ከላይ የተገለፁ ችግሮችን የመቅረፍ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የልቅ ግጦሽን ማስቀረት ሌላው የሚኖረው አካባቢያዊና ሥነ-ምህዳራዊ ጠቀሜታ የእፅዋትና የደን

ልማት ተግባርን በማሳደግ በዚህም ሳቢያ የሚገኙ አካባቢያዊ፣ ሀገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ፋይዳዎች

ናቸው፡፡ የልቅ ግጦሽን አግባብ ባለው አሠራር በመከላከል ሂደት የእንስሳትን ያልተፈለገ ተፅዕኖ

በአካባቢው በማስቀረት በሚከለሉና እንዲያገግሙ በሚደረጉ ተፋሰሶች ውስጥ ተጨማሪ

የማጠናከሪያ አፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ሲከናወኑ የእፅዋትና የደን ዛፎች ሽፋን ይሻሽላል፡፡

የእፅዋት ሽፋን በተሻሻለ ቁጥር የአፈር መሸረሸርን ከመከላከል ባሻገር የሚዘንበውን ዝናብ ወደ

መሬት ውስጥ እንዲሰርግ በማድረግ የውኃ አቅርቦት በመጨመር ሌላ የልማት እድል ይፈጥራል ፡፡

በሌላ መልኩ የሚጨምረው የእጽዋትና ደን ሽፋን ወደ ዓየር የሚለቀቀውን የካርቦን ልቀት

በመምጠጥ የዓየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋምና ለመሰረይ እገዛ ያደርጋል፡፡

3.2 የእንስሳት ምርታማነትን ለመጨመር ያለው ጠቀሜታ

ልቅ ግጦሽ በማይኖርበት አካባቢ አስፈላጊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እፅዋቶች እንዲያድጉ

ስለሚደረግ እንስሳቱ ቀኑን ሙሉ በመዞር ከሚያገኙት መኖ በተሻለ ጥራትና መጠን ይቀርባል፡፡

ይህ በመሆኑም የተሻሻሉና የተለያዩ ንጥረ ነገር ያላቸው የእንስሳት መኖ ስብጥርም እንዲመረት

እድል ስለሚፈጥር ጥራት ያለው የእንስሳት መኖ እንዲቀርብ ስለሚያስችል የስጋም ይሁን የወተት

ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡በተጨማሪ ልቅ ግጦሽን ማስቀረት የእንስሳትን

የእርስ በርስ መዳቀልን በማሰቀረት በዚህ ምክንያት የሚታዩ የምርታማነት ችግር፤ በሽታን

4

ያለመቋቋምና ሌሎች አላስፈላጊ ባህሪያትን የመከላከልና ዝርያ የማሻሻል ሥራንም ለማጎልበት

ያስችላል፡፡

እንስሳትን አስሮ የመመገብ ሥራ በተግባር ሲውል አርሶና አርብቶ አደሩ ብዙና ምርታማ ያልሆኑ

እንስሳትን ከመያዝ ይልቅ ጥቂት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲያረቡ

ስለሚያግዝ ጥራት ያለው የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርቢዉን የገቢ ምንጭ

ያሳድጋል ፡፡

በሌላ መልኩ እንስሳቱ መኖ ፍለጋ ቀኑን ሙሉ ሲዞሩ በሚውሉበት ሂደት የሚመገቡትን መኖ

ሰውነታቸውን ከመገንባትናለወተት ምርት ወዘተ ከማዋል ይልቅ ለመንቀሳቀሻ ኃይል/ጉልበት

ያዉላሉ፡፡ በአስሮ መመገብ ተግባር ይህ ችግር ስለሚቀረፍ እንስሳቱን አደልቦ ለገበያ ለማቅረብ

ጊዜን ከማሳጠሩ በተጨማሪ ሌሎች የእንስሳት ውጤቶች ምርትና ጥራት በከፍተኛ ደረጃ

እንዲያድግ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ- ቆዳና ሌጦ

ልቅ ግጦሽን በማስቀረት ተከልለው እንዲያገግሙ በሚደረጉበት አካባቢዎች ሌሎች የእንስሳት

እርባታ ሥራ እድሎችን ይከፍታል ለምሣሌ የንብ እርባታ የመሳሰሉትን ለማስፋፋት ያግዛል፡፡

በአርብቶ አደር ህ/ሰብ አካባቢ ያለውን በአንሰሳት ቁጥር የተመሰረተ የሀብትና የማህበራዊ ህይወት

የበላይነት አስተሳሰብን በማስቀረት የእንሰሳት ሀብት ልማት ስራዎችን በመቀድ ማከወን ያስችላል

፡፡ሌላው እንስሳት ለመኖ ፍለጋ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ካስቀረን የተለያዩ የአትክልትና

ፍራፍሬ ልማት ሥራ ለመስራት አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፤ ተረፈ ምርታቻዉም ለእንስሳቱ

ምግብነት ስለሚዉል ለምርታማነታቻዉ ማደግ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

3.3 ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ

እንስሳትን አስሮ መመገብ የመኖ አቅርቦትን በመጠንና በጥራት እንዲቀርብ በማድረግ የእንስሳት

ምርታማነት በመጨመሩ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ከላይ ለማስረዳት ተሞክሯል፡፡

ከዚህም ሌላ እንስሳትን አሥሮ/ተቆጣጥሮ መመገብና መንከባከብ በርካታ ምርትን የሚቀንሱና

ድንበር ዘለል በሽታዎችን ለመቆጣጠር ከማስቻሉም በላይ ወደ ውጪ አገር በሚላኩ ምርቶች

ጥራት ላይ በተቀባይ አገሮች ለሚኖረው አሜኔታም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ በሚደረጉ አካባቢዎችም ለንቦች ምግብ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ

የአበባ እፅዋቶች እንዲያድጉ እና እንዲስፋፉ ስለሚያደርግና በቂ መኖ ስለሚያገኙ ተጨማሪ ገቢ

ሊያስገኝ የሚችል የንብ እርባታ በማካሄድ ከአንድ ቀፎ የሚገኘዉን የማር ምርት እንዲጨምር

5

ያደርጋል ፡፡ይህ በመሆኑም አርሶ/አርብቶ አደሩ የገቢ እድሉን እንዲያሰፋ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡

በሌላ መልኩ በእርሻ ማሳ ላይ የጥምር ደን እርሻ የአስተራረስ ዘዴን በማስፋፋት የሚመረተውን

የእንስሳት መኖ የእንስሳት እርባታ በማካሄድ ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የተመረተውን

መኖ ለገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጭ እንዲያድግ አስተዋፅኦ አለው፡፡

በልቅ ግጦሽ ተግባር እንስሳቱን የማገድ ኃላፊነት የሚያርፈው በአብዛኛው በህፃናት እና ሴቶች ላይ

እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ሳቢያም ለትምህርት የደረሱ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ

ይልቅ እንስሳቱን እንዲጠብቁ ይደረጋሉ፡፡ ሴቶችም ቢሆኑ ልጅ ከማሳደግና የቤት ውስጥ አድካሚ

የሥራ ኃላፊነት ባሻገር እንስሳትንም ቀኑን ሙሉ ልጅ አዝለው በማገድ ከፍተኛ የሥራ ጫና

ተሸካሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ስለሆነም ጥቂት ምርታማ የሆኑ እንስሳትን በመያዝ አስሮ የመመገብ

ልምድ ተስፋፍቶ ልቅ ግጦሽን በማስቀረት ህፃናት የትምህርት እድል እንዲያገኙና ጉልበታቸው

ያለ እድሜ እንዳይበዘበዝ በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን ማህበራዊ ችግር ለማቃለል ያስችላል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በእናቶች ላይ የሚደርሰውን የሥራ ጫና በመቀነስ ለልጆቻቸው ተገቢውን

እንክብካቤ እንዲያደርጉና በጓሮ ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ በሌላ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ላይ

እንዲሰማሩ እድል ይፈጥራል፡፡

ከላይ ከተገለጸዉ ሌላ በብዙ የሀገራችን አካባቢዎች እንስሳሳት ተለቀው ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ

እንዲግጡ በሚደረጉበት ተግባር እንስሳት በአጐራባች በሆኑ የሰብል ማሳና በግል በተያዙ የግጦሽ

መሬት ውስጥ በመግባታቸው በአርሶ አደሮች መካከል ግጭት ሲፈጠር ቆይቶል፡፡ አልፎአልፎም

በዚህ ሳቢያ በሚፈጠር ፀብ እርስ በእርስ እስከ መገዳደል የሚደርስ ማህበራዊ ቀውስ ነበረው፡፡

በመሆኑም ልቅ ግጦሽን ማስቀረት በዚህ ረገድ የሚከሰቱትን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል ድርሻ

አለው ፡፡

በሌላ መልኩ ትኩረት የሚሻዉ ጉዳይ እንስሳትን አስሮ በመመገብ ቋሚ የማዋያ ቦታ

እንዲኖራቸው ስለሚደረግ ከእንስሳቱ የሚገኘውን ፍግ አንድ ቦታ በመሰብሰብ ለሰብልና የግጦሽ

መሬቶችን ለምነት ለማሻሻል የሚረዳ ኮምፖስት ዝግጅት የሚያግዝ መሆኑ ነው፡፡ ከእንስሳት ጤና

አኳያም በልቅ ግጦሽ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችንና ጥገኞችን ለመቆጣጠር ሲያስችለን

በሽታዎቹ በመከሰታቸው ምክንያት ለህክምና የሚወጣ ወጪንም ለማዳን ይረዳል እንዲሁም በስጋ

በል የዱር አራዊት የሚደርሰውን ጉዳት ይጠብቃል፡፡

ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በየተፋሰሶቹ የሚገነቡ የፊዚካል አፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች

በእንስሳቱ እንቅስቃሴ የመፍረስና የመጐዳት አደጋ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ

6

ለሥራዎቹ ያወጣው ጉልበት ከንቱ እንዲሆን የሚያደርግና በተደጋጋሚ ጥገና ለተጨማሪ አላስፈላጊ

ሥራ ይዳረጋል፡፡

4. ልቅ ግጦሽን በማስቀረት ውጤታማ የሆኑ ተሞክሮዎች

እንስሳትን አስሮ የመመገብ ልምድ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢዎች የረዥም ዓመታት

ተሞክሮዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሲተገበሩ የነበሩት እንስሳትን አስሮ

አጭዶ የመመገብ ተግባር ቢሆንም አተገባበሩ በክረምት ወቅት የእርሻ ማሳዎች በሰብል

በመሸፈናቸው ምክንያት በዚህ የግብርና የጊዜ ሰሌዳ ወቅት በመተግበር ላይ የተወሰነ ነበር፡፡ በበጋ

ወቅት ግን ሰብል መነሳቱን ተከትሎ ልቅ ግጦሽ ይካሄዳል፡፡ ይህም በክረምት ወቅት የሚከለከለው

የልቅ ግጦሽ ተግባር ከግጦሽ መሬት መመናመንና አብዛኛው የከብቶች መዋያ የነበሩት ተራራማ

የወል መሬቶች ጭምር ወደ እርሻ በመለወጣቸው ምክንያት የመሬት ጥበት በመኖሩ ነው፡፡

በመሆኑም በተለይ የእርሻ በሬዎችን እንደሌሎቹ እንስሳቶች በበጋውም ወቅት አስሮ የመቀለብና

የማደለብ ልምድ በመኖሩ ከአካባቢው ለገበያ የሚቀርቡት የዳልጋ ከብቶች ጥራት ያላቸውና ለሥጋ

ምርት ተፈላጊ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ በሁለቱም ዞኖች

የሚካሄደው የአስሮ መመገብ ልምድ ወጥ በሆነ መልኩ ሥርዓት ተፈጥሮለት የሚከናወን

አልነበረም፡፡

በምርጥ ተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችለው በፕሮጀክቶች በመታገዝ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዶባ ወረዳ

የልቅ ግጦሽን የመከላከል ተግባር በውስን ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ ተደርጐ ውጤታማ በመሆኑ

ወደ ሁሉም የወረዳው ቀበሌዎች እንዲስፋፋ የተደረገው ተሞክሮ ነው፡፡ በወረዳው በሚገኙ

አብዛኛዎቹ ቀበሌዎች ለብዙ ዓመታት የተፈጥሮ ሀብት መከላት ምክንያት የአፈር ለምነት

በመቀነሱ እና ምንጮች በመድረቃቸው ሳቢያ ችግር ላይ ወድቀው ነበር፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች

ተፋሰስን መሠረት ያደረጉ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ልቅ ግጦሽን ከማስቀረት ጋር

ተቀናጅተው ተግባራዊ በመደረጋቸው በአካባቢው የተጐዱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ተደርገዋል፡፡

የተገኘው ውጤትም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ምርጥ ተሞክሮ

ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ልቅ ግጦሽን በማስቀረት ሂደት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወነ

በመሆኑ እና አስተዳደሩንም በሚመለከት ሥርዓት ተዘጋጅቶለት የሚተገበር በመሆኑ ሀገራዊ ልቅ

ግጦሽ የማስቀረት ስትራቴጂ ለመንደፍ መነሻ ሆኖ ማገልገል ይችላል፡፡

ከሌላ አካባቢ በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚችለው በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ዙሪያ ወረዳ ዳቤደንጐሮ

በመባል የሚታወቀውና ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን አካባቢን የሚሸፍን መሬት በመከለል

7

ከእንስሳትና ሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግም የተደረገው ነው፡፡ ይህን የአንድ ንዑስ ተፋሰስ

ተሞክሮ በማየትም አንድ ሙሉ ቀበሌ ልቅ ግጦሽን ማስቀረት ያስቻለበት ልምድ አለ፡፡

በተመሳሳይ ለተሞክሮነት ሊወሰዱ የሚችሉ እንስሳትን አስሮ የመመገብ ተግባር በተለያዩ የሀገሪቱ

አካባቢዎች ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን ስፋት ባለውና አቋም ተወስዶበት፤ አሠራር ተዘርግቶለት

ተግባራዊ የተደረገበት ተሞክሮ ያለው በትግራይ ክልል ነው ማለት ይቻላል፡፡ በክልሉ ከአለፉት

አራት ዓመታት ወዲህ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ

ሥራዎች ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ የፊዚካል የአፈርና ውኃ ጥበቃ ቴክኖሎጂዎች በተተገበሩባቸው

እና ተከልለው እንዲያገግሙ በተደረጉባቸው አካባቢዎች ልቅ ግጦሽ እንዳይኖር የተደረገበት

ተሞክሮ ይጠቀሳል፡፡ ልቅ ግጦሽን ለማስቀረት በተደረገው ጥረትም አተገባበሩ እንደየአካባቢው

ሁኔታ ከቀበሌ ቀበሌ፣ ከወረዳ ወረዳና ከዞን ዞን ልዩነት ያለበትና በተሟላ መልኩ ተግባራዊ

ባይደረግም ትርጉም ያለው ሥራ ግን ተሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑም ልቅ ግጦሽን

በማስቀረት ሊነሳ የሚችለውን የእንስሳት መኖ አቅርቦት ችግር ከተፋሰስ ልማት ሥራው ጋር

በማቀናጀት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በትግራይ ክልል ልቅ ግጦሽን በማስቀረት አስሮና አጭዶ መመገብ ተግባራዊ በተደረጉባቸው

አካባቢዎች በየተፋሰሶቹ ውስጥ በሚፈጠሩ የተፈጥሮ ሀብቶች ለእንስሳት መኖ የሚያስፈልጉ

እፅዋቶችና ቅንጥብጣቢዎች እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡ ሌሎች የልማት እድሎች በመፈጠራቸውም

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የሥራ መስኮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ በተፋሰሶቹ ውስጥ

የተለያዩ ለንብ መኖ የሚሆኑ እፅዋቶች በመፈጠራቸው ሰፊ ሊባል የሚችል ወጣቶችንና ሥራ

የሌላቸው የህብረተሰብ ከፍሎች በንብ እርባታ ላይ በመሠማራታቸው የሥራ እድል እንዲፈጠር

አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ መሬት አልባ የሆኑ ወጣቶችና ሴቶች የዚህ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው

የተረጋገጠበት ተሞክሮ በሌላውም አካባቢ መስፋፋት የሚችል ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው

ህብረተሰቡ ተስማምቶበት የልቅ ግጦሽን ማስቀረት በመቻሉና ወደ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታና

የመሬት አጠቃቀም ተግባር በመግባቱ ነው፡፡ በክልሉ ባለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ በተደረጉ

የተቀናጁ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች እና በተፋሰሶች የላይኛው አካል ላይ የእፅዋት

ሽፋን እንዲጨምር በመደረጉ የዝናብ ውኃ ወደ መሬት እንዲሰርግ የሚያደርጉ ተግባራት

በመከናወናቸው በተፋሰሶቹ የታችኛው አካል የመስኖ ልማት እድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የእንስሳትም

እንቅስቃሴ በመገታቱ በመስኖ የሚለሙ አካባቢዎች ሰብሎች በእንስሳት እንዳይበሉ በማድረጉ

የእርሻ ሥራ ያለ ስጋት እንዲፈፀም አግዟል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ይልቅ ግጦሽን የማስቀረት ተሞክሮዎች በበጐነትና በጠንካራነት የሚታዩ

ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ችግር የሚነሱ ጉዳዮች በህብረተሰቡ ስምምነት ልቅ ግጦሽን በማስቀረት

8

የተፈጥሮ ሀብት እንዲሻሻል በተደረጉባቸው ተፋሰሶች አልፎ አልፎ የሚታየዉ ጭለማን ተገን

በማድረግ አንዳንድ ሰዎች የሚያደርሱት የስርቆት ችግር ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን ህብረተሰቡ

በየአካባቢው በዘረጋቸው አሠራሮች እየፈታቸው የሚገኝበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡

5. ልቅ ግጦሽን የማስቀረት ተግዳሮቶች

በሀገራችን ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ እና ብዙ እንስሳትን ይዞ ማቆየት እንደ ሀብት

የሚታይበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ የእንስሳቱን የመኖ ፍላጐት ለሟሟላት ሲባልም እንስሳቱ በነፃ

እየተንቀሳቀሱ እንዲግጡ ማድረግ በተለመደበት አሠራር ልቅ ግጦሽን ለማስቀረት የሚደረጉ

ጥረቶች እና ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ማድረግ ከችግር ነፃ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገር

ግን በሂደቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማነቆዎችንና ተግዳሮቶችን ከወዲሁ ለይቶ መንቀሳቀሱ አስፈላጊ

በመሆኑ ከተሞክሮ በመነሳት ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ተግዳሮቶች መነሻቸውና ይዘታቸው

ተተንትኗል፡፡

5.1 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች

የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ሳይጨምር በሌሎቹ ብዙ የሀገራችን አካባቢዎች አርሶ አደሩ ከጋማ

ከብት ጀምሮ እስከ ዶሮ ያሉትን ለማዳ እንስሳትን በመያዝ ከእንስሳቱ የሚፈልጋቸውን ሁሉንም

አገልግሎቶች በራሱ ለመሸፈን የመፈለግ አመለካከትና ተግባር አለ፡፡ ብዙውን ጊዜ በተለይ እንደ

በጐችና ፍየሎች ያሉትን አነስተኛ እንስሳት አስሮ የመመገብ ልምድ እምብዛም አይታይም፡፡ ከዚህ

በመነሳትም አንድ ቤተሰብ ከእያንዳንዱ የእንስሳት ዓይነት የሚይዝ በመሆኑ ሁሉንም አስሮ

ለመመገብ ሊቸገር የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ይታሰባል፡፡ ይህ በመሆኑም እያንዳንዱ ቤተሰብ

የሚይዘውን የእንሰሳት ቁጥር በመቀነስ ከትንሽ ቁጥር ነገር ግን ከፍተኛ የሥጋና የወተት ምርት

የሚሰጡትን እንዲይዝ ማደረጉ ግድ ይላል፡፡ አርሶ አደሩ የእንሰሳቱን ቁጥር በመቀነስ የተሻሻለ

ዝርያ ያላቸውንና ምርታማ የሆኑትን ማግኘት ካልቻለ ምናልባት ከብዙ ቁጥር እንስሳት ያገኝ

የነበረው ገቢ ሊቀንስ ስለሚችል ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ በመሆኑም የተሻሻሉ

የእንሰሳት ዝርያዎችን የማቅረብ ስራና ያሉንን የተሻሉ እንስሳትን ዝርያ ማሻሻል ሥራ ትኩረት

ተሰጥቶት ልቅ ግጦሽን ከማስቀረት ተግባር ጋር ተቀናጅቶ እንዲተገበር ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው

የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

እንስሳት የመኖ ፍላጐታቸውን ለማሟላት ሲባል ተለቀው ሲግጡ የነበረበት ተግባር እንዲቀር

ሲደረግ አርሶ አደሮች አስሮ ለሚመግቧቸው እንስሳት መኖ እያሰበሰቡ ማቅረብ ስለሚገባቸው በቀን

ከሚኖራቸው የእርሻ ስራ ጊዜ የተወሰነውን በመኖ ማቅረብ ላይ ማሳለፋቸው የማይቀር ነው፡፡ ይሄ

9

ደግሞ የመኖ አቅርቦቱን አስተማማኝነት እያረጋገጡ መተግበር ካልተቻለ ማነቆ መሆኑ አይቀርም፡

5.2 ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ተግዳሮቶች

እንስሳትን በአንድ ቦታ በማቆየትና መኖን በማልማት የመመገብ ዘዴ ዘመናዊ የእንሰሳት እርባታ

ተደርጐ ይወሰዳል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ወገኖች ይህን በጐ ተግባር በተሟላ መልኩ

በመረዳትም ይሁን ባለመረዳት የማጥላላትና የህብረተሰቡን መብት የተጋፋ ጉዳይ አድርገው

የኘሮፖጋንዳቸው መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ የዚህ አይነት አፍራሽ እና ለልማታችን

እንቅፋት የሆነ ተግባር እነዚህ ወገኖች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ቀደም ሲል በምርጫ 1997

በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ያጋጠመ ችግር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱም የራሳችን መዋቅር

በአንዳንድ አካባቢዎች ልቅ ግጦሽን ለማስቀረት የተከተላቸው ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄዶች ለእነዚህ

ወገኖች አፍራሽ ኘሮፖጋንዳ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የምንከተለው

የስትራቴጂው አፈጻጸም ለእንደዚህ ዓይነት በጐ ያልሆነ ተልዕኮ በር የሚከፍት እንዳይሆን ጥንቃቄ

ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በሌላ መልኩ ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ

የስትራቴጂውን አስፈላጊነትና ለልማታችን ያለውን ጉልህ ጥቅሞች አሳንሶ በማየት ወይም ስራው

አድካሚ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ላይፈፅመው ይችላል፡፡ በአፈፃፀም ሂደት ውስጥ ስትራቴጂውን

በህብረተሰቡ ተሳትፎ አሳምኖ እንዲተገበር ከማድረግ ይልቅ ወደ ማስገደድና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ

መንገድ ለማስተግበር መንቀሳቀስ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ መገንዘብ

ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ልቅ ግጦሽን ከማስቀረት ጋር ተቀናጅተው መተግበር የሚገባቸው

የግብአት አቅርቦት ችግሮች ማለትም የመኖ ዘሮች፤ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች አቅርቦትና

ያሉንን እንስሳት ዝርያ ማሻሻል ፕሮግራም አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ላይ

የመለሳለስና አድምቶ ባለመስራት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሌሎች ችግሮች ናቸው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ አርሶ አደሩን በቅርበት የሚደገፈው ባለሙያ የተሟላ አመለካከትና ክህሎት

ሳይጨብጥ ለአርሶ አደሩ በቂ ድጋፍ ባለማድረጉ የስትራቴጂው ተግባራዊነት ሊሸራረፍ ይችላል፡፡

6. የስትራቴጂው አቅጣጫዎች

ልቅ ግጦሽን የማስቀረት ስትራቴጂ እንደየመሬት አጠቃቀሙ ዓይነት መከተል የሚገባን ሆኖ

እንስሳትን አስሮና አጭዶ መመገብ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን አቀናጅቶ መተግበር ያስፈልጋል፡፡

10

አንዱ ምርታማ የሆኑ እንስሳትን ዓይነትና ቁጥር ከመኖ አቅርቦት ጋር አጣጥሞ መተግበር ሲሆን

ሁለተኛው ደግሞ ከዚሁ ጐን ለጐን የተሻሻሉ የእንስሳትና የመኖ ዝርያዎችን ማቅረብና በአካባቢው

ከሚገኙትም በመምረጥ ወይም ከሌላ አካባቢ አምጥቶ የማላመድና የማሻሻል ተግባር የትኩረቱ

አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የእንስሳት መኖን የማምረት ተግባር እንደ አንድ

የልማት ሥራ በመውሰድ በተከለሉ ተፋሰሶች፣ በእርሻ ማሳ ድንበር ላይ፣ በወንዞች ዳርቻ፣

በቦረቦሮች አካባቢ እና በጓሮ የማልማት የስትራቴጂው አቅጣጫ ይሆናል፡፡ ዝርዝር ስትራቴጂዎቹ

ቀጥሎ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

6.1 ተከልለው እንዲያገግሙ በተደረጉ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች

በተከናወኑባቸው አካባቢዎች የመኖ ምርታማነት የማሳደግ ስትራቴጂ

ህብረተሰቡ በራሱ ጉልበት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በሚያደርግባቸው

ተፋሰሶች እና በሌሎች ከእንስሳትና ሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ በተፈጥሮ እንዲያገግሙ የማድረግ

ተግባር በህብረተሰቡ ሙሉ ፍቃደኝነትና ስምምነት መከናወን እንደሚገባው በመሠረተ ሀሳብ ደረጃ

በሁሉም ዘንድ ግንዛቤ ተፈጥሯል፡፡ ይህንን ግንዛቤ በማሳደግ ወደ ተግባር ሲገባ ከአካባቢዎቹ

የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና ከአካባቢዎቹ በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ጥቅም ማግኘት

ያላባቸው የህብረተሰቡ አካላት የሚያገኙት ጥቅም ፍትሀዊ መሆኑንም ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች እንስሳት እንዳይገቡ ሲከለከሉ ለእንስሳቱ መኖ የሚሆን አጭዶ በመውሰድ

እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡ በዚህ ሂደት ታጭዶ የሚወሰደው የመኖ ዓይነትና መጠን የተጠቃሚውን

ፍላጐት ማሟላቱን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ አጠቃቀሙን በሥርዓት እንዲመራ የማድረግ ስትራቴጂ

መከተል ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተፋሰሶቹ የሚፈጠረውን የልማት እድል

አጠቃቀም በሚመለከተ በሥርዓት የመምራት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የመኖ ምርታማነትን

ማሳደግ ደግሞ የስትራቴጂው አቅጣጫ መሆን ይገባዋል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች

የፊዚካልና የሥነ-ህይወታዊ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ስለሚያካትት የሚመረጡትን የስነ-

ህይወታዊ ቴክኖሎጂዎች እንደየስነ-ምህዳሩ ተስማሚነት ለእንስሳት መኖ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ

የሚችሉትን በልዩ ትኩረት መተግበር ያስፈልጋል፡፡ የዕፅዋት ዝርያዎቹም በተቻለ መጠን ለሁሉም

ዓይነት የእንስሳት ዝርያ (ንብን ጨምሮ) ፍላጐት የሚሆኑ መሆን ይገባቸዋል ይህም ሲባል የሣር፤

የቅጠላቅጠልና የቅንጠባ እጽዋትን ማካተቱን፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን እያንዳንዷ ካሬ ሜትር

የምትሰጠውን የመኖ ምርት መጠን ማሳደግ የሚቻልበትን ተግባራት ሁሉ የመፈፀም አቅጣጫ

መከተል ያስፈልጋል፡፡ በባለሙያ በመታገዝ የብዝሀ ህይወቱን ስብጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ

አረም ነክ የሆኑትን ማስወገድ፣ የውኃ መቋጠሪያ ስትራክቸሮች መጠገናቸውን መከታተል እና

11

በተለይ ደግሞ በእያንዳንዱ የዝናብ ወቅት ማብቂያ ጊዜ የአፈር እርጥበቱን ማቆየት እንዲቻል

የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን አቅጣጫዎች ለመከተል የተከለሉት አካባቢዎች ከጅምሩ ለምን አገልግሎት

እንደሚውሉ የመሬት አጠቃቀሙን በባለሙያ በመታገዝ ከህብረተሰቡ ጋር መወሰን ያስፈልጋል፡፡

ለደን ልማት የሚውል ከሆነ የሚተከሉት ዛፎች የተወሰነ እድገት ደረጃ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ

የመኖ ዕፅዋትን አቀናጅቶ የማልማት አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል፡፡ የእንስሳት መኖ ለማልማት

ከሆነ ዋና ትኩረቱ ይሄ ስለሚሆን አልፎ አልፎ ለጥላና ለሌላ ስነ-ምህዳራዊ ጥቅም የሚሰጡ

እስካልሆነ ድረስ በመኖ እፅዋት ምርታማነት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ዛፎችን አለመትከል ጠቃሚ

ይሆናል፡፡

6.2 በእርሻ ማሳዎች ላይ የምንከተለው ስትራቴጂ

በአርሶ አደሩ በግል የተያዙ ማሳዎች ዋና ትኩረቱ የሰብል ምርታማነትን የመጨመር ጉዳይ ነው፡፡

የማሳዎችን ምርታማነት ለመጨመር ከሚከናወኑ የግብዓት አጠቃቀም ማሻሻያ ሥራዎች ጐን

ለጐን የጥምር ደን እርሻን የማስፋፋት አቅጣጫ በመከተል በገጠር ልማት ፖሊሲዎች፣

ስትራቴጂዎችንና ስልቶች ላይ በግልፅ የተቀመጠውን መተግበር ያስፈልጋል፡፡ ለጥምር ደን እርሻ

የሚመረጡ የዛፍ ዝርያዎች የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉና ተመልምለው ወይም ቅርንጫፎቻቸው

ተቆርጠው ለእንስሳት መኖነት ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ልቅ

ግጦሽ ሲቀር ማሳዎቹ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ስለሚሆኑ ክረምት ከበጋ መኖ ማግኘት ይቻላል፡፡

በሌላ መልኩ በእርሻ ማሳዎች ውስጥ በሚሠሩ የፊዚካል አፈርና ውኃ ጥበቃ ስትራክቸሮች ላይ

የመኖ ሳር፤የቅንጠባ እጽዋት እና ሌሎች የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ የአትክልትና ፍራፍሬ

በማምረት ከእነዚህ የሚገኘው ተረፈ ምርት ለእንስሳት መኖ የሚውልበትን አማራጭ ማስፋት

የስትራቴጂው አካል ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ አርሶ አደር በግል በያዘው ማሳ ላይ ከሰብል ልማቱ ጋር

በማቀናጀት የሚያረባቸውን እንስሳት የመኖ ፍላጐት በበቂ እንዲያሟላ ማድረግ በወል በተያዙ

ተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን ጫና በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ስለሚኖረውም የስትራቴጂው

አካል ተደርጐ መውሰድ ተገቢ ይሆናል፡፡

አርሶ አደሮች በግል በያዙት ማሳ ላይ በፈለጉት መልኩ የመጠቀም መብት ያላቸው ከመሆኑ ጋር

ተያይዞ ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ ከብቶቹን የመልቀቅ ፍላጐት ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን

በማንኛውም ጊዜ አርሶ አደሩ በግሉ በሚጠቀምበት መሬት ላይም ቢሆን የልቅ ግጦሽን ጉዳት

እንዲረዳ በማድረግ እንስሳቱን እንዳይለቅ ማግባባት ያስፈልጋል፡፡ ይልቁንም የሰብል ተረፈ

12

ምርትን በማጠራቀም የሚጠቀምበትን አማራጭ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ አርሶ አደሩ የመኖ ባንክ

ፈጥሮ የሚተገብርበትን አሠራር በትኩረት መተግበር እንደ ዋና ጉዳይ መወሰድ አለበት፡፡

6.3 የእንስሳትን ቁጥር የመቀነስና ምርታማ ዝርያዎችን የማስፋፋት

ልቅ ግጦሽን ለማስቀረት የእንስሳትን የመኖ አቅርቦት በዓይነትና መጠን ማሳደግ የስትራቴጂው

አካል እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡ ይህ ሆኖ ሲያበቃ በቀረበው መኖ ልክ ከእንስሳቱ የሚያገኛቸው

ምርቶች የላቀ ጥቅም የሚሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ካልተቻለ የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ

ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ አርሶ አደሩ የሚይዛቸውን እንስሳት በማደለብ ወይም የወተት

ምርት እና ሌሎች ውጤቶችን በማግኘት ገቢውን ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ምርታማ

ያልሆኑትን እንስሳት ከመያዝ ባህሉ ተላቆ ጥቂት ነገር ግን ምርታማ የሆኑትን ዝርያዎችን

እንዲለምድ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ገበያ ተኮር የሆኑ እንስሳት የማርባት ባህሉን ማሳደግ

የስትራቴጂው ትኩረት መሆን አለበት፡፡

ይህንን አቅጣጫ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል በመጀመሪያ በአካባቢ ካሉ ዝርያዎች የተሻሻሉትን

በመምረጥ መሆን ይገባዋል፡፡ የወተት ምርት የሚሰጡትን ካልሆነ ቶሎ ቶሎ እያደለበ በፍጥነት

ወደ ገበያ የሚያቀርብበትን አቅጣጫ መከተል ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ብዙ ቁጥር ያለው የቀንድ ከብት በመያዝ ያገኝ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ

ጥቅም በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እንደ ዶሮ እና ንብ እርባታ ያሉትን እንዲለምድ

ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ተግባር ከዓየር ንብረት ጋር ተጣጥሞ እንዲተገበር የተዘጋጀውን

የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ መታየት አለበት፡፡ በስትራቴጂው

መሠረት ከእንስሳት ልማት አኳያ ከምንከተላቸው አቅጣጫዎች መካከል ዋነኛ ሆኖ የተቀመጠው

የእንስሳትን እሴት በመጨመር ላይ የተመሠረተ ውጤታማነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ሲባልም

የቀንድ ከብቶችን ቁጥር የመቀነስ፣ ዝርያዎችን በማሻሻል ምርታማ ማድረግ፣ ሌሎች እንደ ዶሮ

እርባታ ያሉትን መስኮች ማስፋፋት፣ የእርሻ በሬዎችን ለመቀነስ አነስተኛ የእርሻ ማረሻ

ማሽነሪዎችን የማስፋፋት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም ልቅ ግጦሽን በማስቀረት የአረንጓዴ

ኢኮኖሚውንም ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ አቀናጅቶ ለመተግበር ዓይነተኛ ጥቅሞች ይኖሩታል

ማለት ነው፡፡

በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ አንድ ግልፅ የተደረገው ጉዳይ አብዛኛዎቹ የሀገራችን

የቀንድ ከብቶች ዝርያዎች የተመገቡትን መኖ ወደ ጠቃሚ የሰውነት ግንባታ ንጥረ ነገር

የመለመጥ ተፈጥሮአዊ ባህሪ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም የተመገቡትን ነገር አብዛኛውን

13

በዓይነ-ምድር መልክ ስለሚያወጡት ዓየርን በመበከል አስተዋፅኦ ያለውን ሚቴን (Methane)

የሚባል ጋዝ ወደ ዓየር ይለቃሉ፡፡ በሌላ መልኩ የሚሰጣቸው መኖ ውጤታማ አይደለም ማለት

ነው፡፡ በመሆኑም ውጤታማ የሆኑ የእንስሳት ዝርያዎችን የማቅረብና የማስፋፋት ተግባር በውስን

ቦታ ተመርቶ የሚቀርበውን መኖ ውጤታማ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብሎ

ማሰብ ይቻላል፡፡

6.4 የእንስሳትና የመኖ ቴክኖሎጂዎችን አቀናጅቶ የመተግበር

አብዛኛው የሀገራችን አርሶ አደር የኢኮኖሚ ፍላጐቱንና የእርሻ ሥራውን ለማከናወን እንዲሁም

የእርሻ ምርቱን ለማጓጓዝ የሚያስፈልጉትን የጋማ ከብቶች ሳይቀር ሁሉም እንዲኖሩት የማድረግ

ልምድ አለው፡፡ ይህ ልምድ በራሱ ጉዳት ያለው ባይሆንም የሚያረባቸው እንስሳት በቂ መኖ

ከመኖር ጋር ተቀናጅቶ ያለመተግበሩ ግን ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ አርሶ አደሩ የሚይዛቸው

እንስሳት ምርታማ የሆኑና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ

እንደ እንስሳቱ ዓይነትና ዝርያ ተስማሚ የሆኑ የመኖ ቴክኖሎጂዎችን አቀናጅቶ መተግበር

የስትራቴጂው አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ አኳያ በወል በተያዙ እና በተከለሉ አካባቢዎች የሚመረቱትንም ሆነ በግል የእርሻ ማሳ

የሚለሙትን የእንስሳት መኖ ቴክኖሎጂዎች እንደ አስተዋፅኦዋቸው አሰባጥሮ ማልማት

ያስፈልጋል፡፡ ከፍተኛ የወተት ምርት የሚሰጡትን እና የሰውነት ገንቢ የሆኑ የመኖ ዝርያዎችን

በመለየት ከዓላማው ጋር አጣጥሞ ማምረት ያስፈልጋል፡፡ ሌላውየመኖ መገኛ ምንጮችን በሰፊው

የመጠቀም አቅጣጫ መከተል አስፈላጊ ነው ፡፡ይህም ለምሳሌ በአገራችን ከፍተኛ የቅባት ሰብሎች

እንደሚመረቱና በየዓመቱ ከፍተኛ ምርት በጥሬው ወደ ውጪ እንደሚላክ የሚታወቅ ሲሆን እነዚህ

የቅባት እህሎች አገር ውስጥ ቢጨመቁ /ኘሮሰስ ቢደረጉ/ ተረፈ ምርቱ / ፋጐሎው/ ለእንሰሳት

መኖነት እንዲውል ቢደረግ የመኖ አቅርቦትንና ጥራትን ከማሻሻልና እንዲሁም የእንሰሳት

ምርታማነትን በመጨመር ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍያለ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ

መልኩ እንደ ፍየልና በጐች ያሉ አነስተኛ እንስሳትን ፍላጐትና የቀንድ ከብቶችን የአመጋገብ

ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ መኖ ዓይነት የማምረት አቅጣጫ መከተል ግምት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ይህ ደግሞ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፓኬጆችን በማዘጋጀት አቀናጅቶ ተግባራዊ ማድረግን የሚጠይቅ

ይሆናል፡፡

14

6.5 ሌሎች አገልግሎቶችን አቀናጅቶ ተግባራዊ የማድረግ አቅጣጫን መከተል

እንስሳትን አስሮ አጭዶ የመመገብ ስትራቴጂ ለመከተል ከመኖ አቅርቦትና የእንስሳት ቁጥር

መቀነስና ዝርያ ማሻሻል እንዲሁም ሌሎች ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች ተመላክተዋል፡፡ በሌላ

መልኩ ከላይ ከተጠቀሱት ስትራቴጂዎች በተጨማሪ የእንስሳት መጠጥ ውኃ አገልግሎት መስጫና

ውኃ ፍለጋ በሚል ሰበብ ሊከሰቱ የሚችሉ የእንስሳት እንቅስቃሴን ፈር ለማስያዝ የሚያስችሉ

ተግባራትን አቀናጅቶ መተግበር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ውኃ

በተገኘበት ቦታ ሁሉ እንስሳትን ለማጠጣት ሲባል በመስኖ አውታሮችና የተከለሉ አካባቢዎች ላይ

ተፅዕኖ እንዳይፈጠር በጥናት ላይ የተመሠረተ የመጠጥ ውኃ መጠቀሚያ ቦታዎችን በመምረጥ እና

የመጠጥ ውኃ አገልግሎት መስጫ ቦታዎችና መዳረሻ መንገዶችን በመወሰን መተግበር የመሬት

መከላትን ለመቀነስ ዓይነተኛ ድርሻ አለው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የእንስሳት የህክምና መስጫ

ቦታዎችንም እንዲሁ አቀናጅቶ ተግባራዊ ማደረግ ሊተኮር የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

7. የስትራቴጂው የአፈፃፀም ስልቶች

7.1 የህብረተሰቡን ሙሉ ተሳትፎ እና ስምምነት ላይ በመመስረት የመተግበር

ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማና ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ለማስፈን

እና በስርዓት የሚመራ የመኖ አቅርቦት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል ሙሉ

ተሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሀገራችን እንስሳትን በነፃ ለቆ የመኖ ፍላጐትን የማሟላት ልምድ

ከጥንት ጀምሮ ተያይዞ የመጣ በመሆኑ ልቅ ግጦሽ እንዳይኖር የማድረግ ጥረት እንዲህ ቀላል

አይሆንም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተውን የህብረተሰብ ክፍል በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ የመፍጠርና

በአመለካከት የሚኖሩትን ችግሮች ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ውይይቶችን የማድረግ ጥረት ይጠይቃል፡

፡ እንስሳትን አስሮ የመመገብ ተግባር የሚኖሩትን ጥቅሞች በማሳየት ህብረተሰቡ በራሱ ተወያይቶ

እንዲያምንበት ማድረግ የመጀመሪያው የአፈፃፀም ስልት መሆን አለበት፡፡ ስትራቴጂው እንደ

አቅጣጫ ሲወርድ አስፈፃሚው አካል ቀላል ነው ብሎ የሚያስበውን መንገድ መከተሉ የማይቀር

ስለሚሆን በምንም መልኩ የአስገዳጅ እና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድን መከተል መኖር የለበትም፡፡

ህብረተሰቡ ጥቅሞቹን የሚረዳ ከሆነ ለመፈፀም ወደ ኋላ እንደማይል ከሌሎች ተግባራት ተሞክሮ

መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም መዋቅራችን ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ በራሱና በራሱ

ተሳትፎ ብቻ እንዲፈፅመው አመቺ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ያለፈ ተፅዕኖ ከማድረግ መቆጠብ

የግድ ይላል፡፡ ህብረተሰቡ በውይይት ወደ ስምምነት እንዲመጣ የተቻለውን እገዛ ግን ማድረግ

15

ይገባል፡፡ የህብረተሰቡ ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው እና በውሎ ማደር እንዳይዋዥቅ ሥርዓት

እንዲበጅለት ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

7.2 በየደረጃው ላሉ አስፈፃሚ አካላት ግንዛቤ መፍጠር

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ከእንስሳት እርባታ ጋር አቀናጅቶ የመፈፀም ጉዳይ በእውቀት እና

በአመለካከት የተካነ አመራርና ባለሙያ ይጠይቃል፡፡ ስትራቴጂው ወደ ተግባር ሲሸጋገር

ህብረተሰቡን በማሳተፍና ንቅናቄ በመፍጠር በሥርዓት የሚመራው እና የሚደግፈው አስፈፃሚው

አካል መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ በየደረጃው የሚገኘው አመራር የአመራር ሚናውን እንዲወጣ

እና ባለሙያውም እንዲሁ የተሟላ ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ በስትራቴጂው ላይ ግልፅነት

እንዲፈጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አመራሩና ባለሙያው ድርሻውን በመወጣት ውጤት

እንዲመዘገብ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በአመለካከቱና በክህሎቱ ከህብረተሰቡ አንድ ደረጃ ቀድሞ

ሲገኝ ነው፡፡ በመሆኑም አስፈፃሚው አካል በመጀመሪያ አምኖበት እንዲፈፅም የማድረግ ስልት

መከተል ያስፈልጋል፡፡

7.3 መልካም ተሞክሮዎችን የማለዋወጥ ስልት

ህብረተሰቡ በቃል ከሚነገረው ይልቅ በተግባር ባያቸው ጉዳዮች ያምናል፡፡ አስሮ በመመገብ

የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎችንና ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግሙ

ተደርገው ሌሎች የልማት እድሎች የተፈጠሩባቸውን ተሞክሮ በመለየት ግንዛቤ እንዲፈጠር

የማድረግ ስልት መከተል ያስፈልጋል፡፡

ተሞክሮዎቹ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ተግባራትን በማከናወን ይህንኑ አካባቢ በመከለል

በስነ-ምህዳሩ ላይ የተገኘውን ለውጥና ውጤት የሚያሳይ ከመሆኑ ባሻገር በእንስሳት ልማት፣

በመስኖ የማልማት እድል መፈጠሩን፣ የውኃ አቅርቦት የተሻሻለ መሆኑን እና ሌሎች በተፈጠሩ

የልማት እድሎች ህብረተሰቡ ያገኘውን ጥቅም ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን ይገባዋል፡፡

7.4 በየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የማድረግ

በአንዳንድ አካባቢዎች ውስን በሆነ መልኩ እንስሳትን አስሮ የመመገብ ልምዶች መኖራቸው

አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው በሐረርጌ አካባቢ በክረምት ወቅት ያለው ልምድ ነው፡

፡ በዚህ አካባቢ በክረምቱ ተግባራዊ የሚደረገውን ልምድ በበጋውም ወቅት እንዲፈፀም ለማድረግ

ህብረተሰቡን ለማሳመን የቀለለ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በሌላ መልኩ በህብረተሰብ ተሳትፎ

16

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተካሄደባቸውን አካባቢዎች ለመከላከል ሲባል አስገዳጅ ሁኔታዎች

መፈጠራቸው ስለማይቀር በእነዚህ ቦታዎች ፈጥኖ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡

አንዳንድ አካባቢዎች ከመሬቱ ጥበት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ አነስተኛ ቁጥር ያለው እንስሳት

እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አካባቢዎች ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግ

የቀለለ ሊሆን ስለሚችል ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በአንፃራዊነት በእያንዳንዱ

አባወራ/እማወራ የሚያዘው እንስሳት ቁጥር ከፍ ባለበት ቦታ የእንስሳቱን ቁጥር ከመኖ አቅርቦቱ

ጋር አጣጥሞ የማስኬድ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ሲባልም አስሮ መመገብን ተግባራዊ ለማድረግ

የእንስሳቱን ቁጥር መቀነስና ለማካካሻነት የተሻለ ምርት የሚሰጡትን ዝርያዎች ፈጥኖ ማቅረብ

ማስፈለጉ ስለማይቀር ስትራቴጂውን በአንዴ ለመተግበር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በመሆኑም በእንደዚህ

ባሉ አካባቢዎች ቀድሞ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጐት ያላቸውን አርሶ አደሮች ላይ በመሥራት

ሌላው ከእነሱ እየተማረ በሂደት የሚፈፀምበትን ስልት መከተሉ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

7.5 የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ መተግበር

በስትራቴጂው ተግባራዊ ሂደት ውስጥ በየደረጃው የተሟላ አፈፃፀም እንዲመዘገብ የመከታተልና

ከሚያጋጥሙ ችግሮች በመነሳት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የማድረግ ስልት መከተል ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ረገድ ክትትል እና ድጋፍ የሚፈልጉትን ጉዳዮች ከወዲሁ ለይቶ ግልፅ በሆነ መለኪያ

በማስቀመጥ መፈፀም ያስፈልጋል፡፡

በዋናነት በስትራቴጂው ላይ የተቀመጡት አቅጣጫዎች ተቀናጅተው መተግበራቸውን፣ ህብረተሰቡ

የተሟላ ግንዛቤ ፈጥሮ እንዲተገብረው መደረጉን፣ በአስፈፃሚዎች ዘንድ የሚታዩትን ዝንባሌዎች

ተከታታይነት ባለው መልኩ በመለየት ፈጥኖ የማስተካከል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ከክትትልና ድጋፍ አኳያ ሦስቱን መንገዶች ማለትም በሪፖርት፣ በሱፐርቪዥንና በመድረክ

የመገምገም አግባብ አሟልቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

7.6 ተግባራዊ ሥራው በዕቅድ እንዲመራ ማድረግ

ይህ ተግባር ወደ መሬት መውረድ የሚችለው በስትራቴጂው ላይ የተቀመጡትን ጉዳዮች ወደ

ዝርዝር ተግባራት በመለወጥ በየአካባቢው በሚዘጋጁ የልማት ዕቅዶች ውስጥ ተካተው ሲፈፀሙ

ነው፡፡ በመሆኑም ስትራቴጂው ሙሉ በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፈፀም ስለማይችል የተራዘሙ

ዓመታት መውሰዱ ስለማይቀር በአጭር፣ መካከለኛና ረዥም ጊዜ ዕቅዶች ተዘጋጅተው መከናወን

አለባቸው፡፡ በየደረጃው በየዓመቱ በሚዘጋጁ ዕቅዶች ውስጥ እየተካተቱ የሚተገበሩበትን ስልት

መከተል ያስፈልጋል፡፡

17

8. የስትራቴጂው የአፈፃፀም መርሀ ግብር

ተ.ቁ. ተግባራት ፈፃሚው አካል የሚፈፀምበት ጊዜ 1 በግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛው አመራር ደረጃ

መግባባት መፍጠር የማኔጅመንት አባላት እስከ መጋቢት 30/2004

2 ስትራቴጂውን በባለድርሻ አካላት ማስተቸትና ማዳበር

የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ እስከ ሚያዝያ 20/2004

3 ስትራቴጂውን የመጨረሻ ሰነድ ማጠናቀቅ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ እስከ ግንቦት 15/2004

4 በየደረጃው ላሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት

የተፈጥሮ ሀ/ል/ጥ/አ እና የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት

እስከ ሰኔ 15/2004

5 ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ ክልሎች ከሐምሌ 1/2004 ጀምሮ

6 አፈፃፀሙን መከታተልና ግምገማ ማድረግ ግብርና ሚ/ር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎችና ባለድርሻ አካላት

ከሐምሌ 1/2004 ጀምሮ ቀጣይነት ባለው